በሞንትሪያል ከተማ ኑሮአቸውን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ፤ እምነታቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና የሆነ በተለይ፤ ቁጥራቸው በአንጻራዊነት አነስተኛ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ቆይቷል። ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖቹ ተሰባስበው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ለመመስረት ጊዜ ወስዶባቸዋል። እ. ኤ. አ. በ1990 ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በወቅቱ ህልውና በነበረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጽህፈት ቤት ውስጥ ይገናኙ ከነበሩት ኢትዮጵያዊያን ጥቂት ወጣት አርቶዶክስ ክርስቲያኖች በመሰባሰብ በግለሰብ ቤት በህብረት ጸሎት ማድረግ ጀመሩ። ከጊዜ በኋላም ከጥቂቶቹ ውስጥ በተወሰኑ ግለሰቦች ጠንካራ ግፊት ቤተክርስቲያን ለመመስረት ሃሳብ መለዋወጥ ጀመሩ። ሃሳቡን ወደተግባር ለመለወጥም ጥር 7 ቀን 1987 ዓ. ም. በዚያው በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጽህፈት ቤት ከሃያ እስከ ሰላሳ የሚደርሱ አርቶዶክሳዊያን ተገናኝተው የቤተክርስቲያን መስራች ስብሰባ አደረጉ። የሰበካ ጉባኤም ተዋቅሮ የመጀመሪያ አባላቱ ተሰየሙ።
ቀጣዩ ፈተና የጸሎት ስፍራ እና ጸሎት የሚመሩ ቢቻል ካህን አለዚያም የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ያላቸው በጎ ፈቃደኞችን ማግኘት ነበር። ጸሎት ለመምራት በጎ ፈቃደኞች ተገኙ፤ ለጸሎት ቦታም በጊዜው የሶሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ምድር ቤትን ከጥር 15 ቀን 1987 ዓ. ም. ጀምሮ በመከራየት የሰንበት ሳምንታዊ የጸሎት መርሐ ግብር ተጀመረ። የታቦት ስያሜ ለመስጠትም ሦስት ጊዜ ዕጣ እንዲወጣ ተደርጎ በሚገርም ሁኔታ ሶስቱንም ጊዜ “መድኃኔዓለም” የሚለው ስለወጣ በዚሁ ውጤት መሠረት ቤተክርስቲያኑ የሞንትሪያል መድሃኔአለም ቤተክርስቲያን በሚል ስያሜ ተቆረቆረ። ከዚያ ቀደም ሲል እ. ኤ. አ. በ 1991 ቶሮንቶ ከተማ ወስጥ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በካናዳ” በሚል የተመሰረተ እና በኦንታሪዮ መንግስት ህጋዊ እውቅና ያገኘ ሃይማኖታዊ ተቋም ተፈጥሮ ስለነበረ፤ የሞንትሪያል መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በዚያው ተቋም ሥር እንደ ቅርንጫፍ ተደርጎ እንዲደራጅ ሆነ።
በጥቂቶች የተጠነሰሰው፣ ከአንድ ምድር ቤት ወደ ሌላው በኪራይ ሲወጣ ሲወርድ የነበረው የሞንትሪያል መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከጠንካራ ያላሰለሰ ጸሎት፣ የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራሞችና ከሌሎች አጎራባች ከተሞች ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያዊያን በተገኘ ድጋፍና ቸርነት ጭምር ውጣ ውረዶቹን አልፎ፤ አቅሙ ጎልብቶ ዛሬ በግዥ የተገኘ የራሱ ቤተክርስቲያን፣ ቢያንስ አንድ ካህን፣ የተወሰኑ ዲያቆናት ያለው እና በሃይማኖታዊ የረድኤት ድርጅትነት ተመዝግቦ የራሱ ህጋዊ እውቅናን ይዞ የሚንቀሳቀስ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ነው።